
ስትራቴጂ ጽንሰ ሀሳቡ የመጣው ከውትድርና ወይም ጦርነት ነው። ለዚህ ነው ስለስትራቴጂ ሲነሳ ሁልጊዜ በተቀናቃኝ ላይ ብልጫ ከመያዝ አንጻር የሚሆነው። ምክንያቱም በመሠረቱ ስትራቴጂ ማለት በተቀናቃኝ ላይ የመጨረሻውን የድል ብልጫ መውሰድ ማለት ነው። ነገር ግን ስለስትራቴጂ ማውራት እና ስትራቴጂ ቀርጾ በተግባር ላይ ማዋል ለየቅል ናቸው።
በዚህ ጹሁፍ ስለ ስትራቴጂ ዓምስት ጉዳዮችን እዳስሳለሁ፤
፩) ስትራቴጂ ለዘላቂ አሸናፊነት የግድ ያስፈልጋል፤
፪) ስትራቴጂ መሪነትን ይፈልጋል፤
፫) ስትራቴጂ እና ተጽዕኖ መፍጠር የማይነጣጠሉ ናቸው፤
፬) ታላላቅ ስትራቴጂዎች ግባቸውን እንዲመቱ የተከታዮች እና የመሪዎች ጽናት ምሰሶ ነው፤
፭) ስትራቴጂ በየጊዜው ራሱን ከሁኔታዎች ጋር ማስማማት መቻል አለበት፤
፩) ስትራቴጂ ለዘላቂ አሸናፊነት ወሳኝ ነው፤
በውትድርና መጥፎ ስትራቴጂ ወይም ስንኩል ስትራቴጂ ሲኖርህ ግልጽ ላልሆነ ፖለቲካዊ ግብ ትዋጋለህ፣ የአቅርቦት እና የሪሶርስ እጥረት በየጊዜው ያጋጥምሃል፣ ያለአቅምህ ትለጠጣለህ ከዛም “utopia” የሆነ ፈጽሞ የማይሳኩ ግቦች ይኖሩሃል። ይሄ የመጥፎ ስትራቴጂ ወይም የስንኩል ስትራቴጂ ውጤቶች ናቸው። በቢዝነስ ተቋሞችም ውስጥ ተመሳሳይ ነው። የቢዝነሱ ግብ እና አቅም እና ችሎታ ያላቸው ሠራተኞች የሚያጠፉት ጊዜ የተራራቀ ነው። ቢዝነሱ ያለአቅሙ ይለጠጣል፣ በሁሉ ነገር ይነከራል፣ ሁሉን ነገር ለማግበስበስ ይጥራል።
የስትራቴጂክ ስህተት እና የኦፕሬሽን ስህተቶች ውጤታቸው የተለያየ ነው። ስትራቴጂው ጥሩ ሆኖ ኦፕሬሽኑ ላይ ስህተት ቢሰራ ማረም በጣም ቀላል ነው። የተሳሳተ ስትራቴጂ ኖሮ ግን ኦፕሬሽኖችህ ቢሳኩ እንኳ እምብዛም ጥቅም የለውም። ስለዚህ ሳስብ ዘወትር እንደምሳሌ የሚመጣልኝ ጌታችን በስሙ አጋንንት ያወጡትን ሰዎች ያላቸው ነው። “ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን ፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን ፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” እነዚህ ሰባኪያን ኦፕሬሽን ሌቨል (level) ላይ የተሳካ ሥራ የሠሩ ነበሩ፣ ብዙዎች ማሳካት ያልቻሉትን ነገር የፈጸሙ ነበሩ። ነገር ግን ያ ሁሉ በተሳሳተ ዓላማ ላይ የቆመ ስለነበረ አላውቃችሁም ተባሉ።
እኔ ይሄን ለስትራቴጂ ጥሩ ምሳሌ አድርጌ የምወስደው በሕይወት ብዙዎቻችን እንደዛ ስለሆንን ነው። ገንዘብ ማግኘትን ስትራቴጂክ ግባቸው ያደርጉና በመጨረሻ ግን ቤተሰብ አልባ እና ጤና አልባ የሚሆኑ ሰዎች የስትራቴጂ ስንኩልነት የገጠማቸው ናቸው። በሀገር ደረጃ ደግሞ የትግራይ ጦርነት ትልቁ የስትራቴጂ ውድቀት የታየበት ነበር። መቀሌ መግባት ኦፕሬሽን ማሳካት እንጂ ስትራቴጂ አልነበረም፣ በዚህም ምክንያት ያ ጦርነት ሀገሪቷን ያደማ፣ ቤተክርስቲያንን የከፈለ፣ ማንም ያላተረፈበት ሆነ። መንግስት በአማራ ክልል የተከተለው የትጥቅ አስፈታለው ኦፕሬሽንን ተመልከቱ፦ ምን ነበር ስትራቴጂው? ከዛ ምን አስከተለ? ምን ላሳካ ብሎ ትጥቅ ካልፈታችሁ አለ? አሁን የተከሰተውን እና ማጠፊያ ያጣውን መዓት ተመልከቱ። ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቶ እና ከፍተኛ ጊዜ እና ገንዘብ ተርከፍክፎባቸው የሚደገሱ የመዝመሩ፣ የጉባኤ ድግሶች የስትራቴጂ አለመኖር ወይም የመጥፎ ስትራቴጂ ውጤቶች መሆናቸውን ለማወቅ ብዙ ራሱ ሳንቆይ ከዛ በኋላ የሚከሰቱ ልዩነቶችን ማየት ብቻ ይበቃል። ምንድነው ያስገኙት ውጤት? የወጣባቸው ልፋት እና የተለወጠው ነገር ይመጣጠናል? ምንድነው የምር ያሳካነው? በመጨረሻ እነዚህን ሁሉ ከምን አንጻር መዝነናቸው ስትራቴጂው ልክ ነበር ወይም አይደለም እንበል? የማይመዘን፣ የማይገመገም እና የመመዘኛ እና የመገምገሚያ መስፈረት ያላስቀመጠ ስትራቴጂ ገና ከመነሻው ችግር ያለበት ነው።
መጥፎ ስትራቴጂ ኖሮን በኦፕሬሽ ጉዳዮች ላይ መከራከር ጊዜ ማጥፋት ነው። እኔ ብዙ ጊዜ ራሴን ከእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ማራቅን ነው የምመርጠው ፥ ትልቁን ስዕል ለማየት ፍቃደኛ የሆነ አዕምሮአዊ ክህሎትን ማሽተት ካልቻልኩ። ምክንያቱም የተሳሳተ ስትራቴጂ ኖሮ ስለኦፕሬሽን ማውራት ፥ መኪና እንደሚያባርር ውሻ መሆን ነው። መኪናውን ቢደርስበትም ውሻው ምንም አያደርገውም። ነክሶ አያደማው፣ ቦጭቆ አይበላው።
ጥሩ ስትራቴጂ ዓላማን ከተግባር ጋር የሚያዋህድ ነው። ሁለቱን ማጋባት ሲችል ስትራቴጂው ጥሩ ነው ይባላል። ይሄ ማለት ካለን አቅም፣ የሰው ኃይል፣ ሪሶርስ እና ሁኔታ ጋር የተዛመደ ተግባሮችን ማሳካት ከምንፈልገው ዓላማ ጋር ስንቀርጽ ጥሩ ስትራቴጂ ይባላል።
በመነሻዬ እንዳልኩት ስትራቴጂ ተቀናቃኝ ባለበት ሁኔታ የሚቀረጽ እና መነሻውም ከጦርነት ነው።
ስለዚህ ስለስትራቴጂ ስናስብ የግድ ከግንዛቤ መውሰድ ያሉብን ሦስት ነጥቦች አሉ፤
1) የኛን መጎዳት ወይም መክሰር የሚፈልግ ጠላት ወይም ተቀናቃኝ እንዳለን ማመን ያስፈልጋል።
በዚህ ዓለም ላይ ጦርነት ፈጽሞ ሊቆም እንደማይችል ማመን ከሞኝነት የመላቀቂያ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። በተመሳሳይ ዓላማ አንግበን፣ አንዳች ነገር ለማሳካት ስንነሳ በሁሉም አቅጣጫ ጠላቶች እንደሚነሱብን መቀብል የተግባራዊ አስተሳሰብ ጅማሮ ነው። የእኛ መነሳት ወደድንም ጠላንም የሚጎዳው አካል ይኖራል። ያ አካል በቻለው መጠን ይዋጋናል። የእርሱ የበታች አድርጎን ለማቆየት ወይም ለማጥፋት ይሰራል። ስለዚህ ስትራቴጂ ይሄን ሁልጊዜ ከግንዛቤ መውሰድ አለበት።
2) ስትራቴጂ የሚጸናባቸው ግምቶች ለጥሩ ስትራቴጂ እጅግ ወሳኝ ናቸው። ማንኛውም ስትራቴጂ ሲቀረጽ ስለራስም ሆነ ስለተቀናቃኝ ወይም ከኛ ውጪ ስላሉ ነገሮች ጠንቅቀን አናውቅም። ስለዚህ ስትራቴጂያችን ከሞላ ጎደል በግምቶች (assumptions) ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ የስትራቴጂያችን ጥራት በግምቶቻችን ጥራት ላይ ይመረኮዛል። በውትድርና ውስጥ እነዚህን ግምቶች በስለላ ተቋሞች በኩል ሲገኝ፣ በግለሰብ ሕይወትም ሆነ በተቋሞቻችን ስለተቀናቃኞቻችን ያለንን እውቀቶች የምንሞላበት መንገዶች ሊኖሩን ይገባል። አለበለዚያ የሚኖረን ስትራቴጂ ሳይሆን ህልም እና ርዕይ ነው።
3) ጥሩ ስትራቴጂ በአንድ ሀሳብ፣ መሳሪያ ወይም ግለሰብ ብቃት ወይም አቅም ላይ የተንጠለጠለ ፈጽሞ መሆን የለበትም። የትኛውም ጥሩ የውትድርና ስትራቴጂ ባሉት ጥቂት መሳሪያዎች (ከጠላት በሚሻሉ) ላይ ተንጠልጥሎ ተሳክቶ አያውቅም። ወይም በአንድ ግለሰብ ላይ ተመርኩዞም ዘላቂ አሸናፊነት አይገኝም። ከታዋቂ ጄኔራሎች እና የጦር መሪዎች ጀርባ ቀላል የማይባሉ ስትራቴጂክ አሳቢዎች እና የኦፕሬሽን አስፈጻሚዎች አሉ። ዓለም ልብወለድ እና ድራማ ስለሚወድ አንድ ናፖሊዮ፣ አንድ አሌክሳንደር፣ አንድ ምንሊክን ማድነቅ ይወዳል እንጂ ከእነዚህ ምርጥ የጦር ጄኔራሎች ጀርባ ከእነሱ የማይተናነሱ ሌሎች ምርጦች ነበሩ። በተመሳሳይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትም ሆነ ቀዝቃዛው ጦርነት አሜሪካ ከጀርመን ወይም ከራሺያ የሚልቁ ምርጥ መሳሪያዎች ስላሏት አይደለም ያሸነፈችው። ይልቁስ ብዙ ነገርን ታሳቢ ባደረገ እና ውህደት (synergy) በፈጠረ፣ በየጊዜው ራሱን እያሻሻለ እና እየተማረ በሚሄድ ስትራቴጂ እና መሪዎች ምክንያት ነው ያሸነፈችው። ተቀናቋኇቿ ደግሞ ይሄ አልነበራቸውም።
በግል ሕይወትም ከችግር ለመውጣት ገንዘብ የሚጠይቅ ሰው እምብዛም ከችግር እንደማይላቀቅ አምናለሁ። ለእንደዚህ ዓይነት ሰውም ሆነ ተቋሞች የሚሰጥ ገንዘብ ከብክነት ብዙ ለይቼ አላየውም። ምንም ጥርጥር የለውም ገንዘብ በኦፕሬሽን ላይ የሚያስፈልግ ትልቅ ሪሶርስ ነው። ነገር ግን ገንዝብ ስትራቴጂ ሆኖ አያውቅም። በጎስቋላ ሕይወት ውስጥ ያለ ግለሰብም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያሉ ተቋሞች የገንዘብ ችግር አይደለም ያለባቸው። እንደውም ገንዘቡ የችግሩ አካል ሆኖ እንጂ የምንመለከተው። እንደ ኮዳክ ካሜሬ እና ኖኪያ ስልክ የመሰሉ ኩባንያዎች መሪዎቻቸው እያለቀሱ ከገበያ የወጡት የገንዘብ እጥረት ስለነበረባቸው አልነበረም። ስለዚህ ስለጥሩ ስትራቴጂ ስናስብ ገንዘብ ስላለን፣ ወይም አንድ ምርጥ ሰው በመካከላችን ስላለ፣ ወይም ጥሩ መሳሪያዎች ስላሉን ስትራቴጂያችን ይሳካል ብለን ማሰብ የለብንም።
Comentarios