ርጋታ
- Mulualem Getachew
- Apr 6
- 3 min read

ብሩስ ሊ “በሕይወቴ ረዥም ጊዜ ለመማር የወሰደብኝ ግን ደግሞ ለማሸነፌ መሰረታዊ የሆነው ነገር ርጋታን መጎናጸፍነበር” ብሏል። በዚህ ዘመን ከምንም ነገር በላይ እያጣን ያለነው ነገር ርጋታ ይመስለኛል። ሁሉንም ነገር እኛ ባልነው ሰዓት እና ጊዜ ብቻ ማከናወን መፈለግ። ዛሬ ወይም በጣም አጭር በተባለ ጊዜ ውስጥ ሀብታም መሆን። ወይም አዋቂ መሆን።ወይም ታዋቂ። ይሄን ለመከወን ደግሞ ሁሉንም አቋራጭ መንገዶች ለመጠቀም መፈለግ። በዚህ ፍላጎታችን መስመር ውስጥ እንከን ከገጠመን ሰማይ ምድሩ ነው የሚገለባበጥብን።
መስከን የሚባል ነገር ርቆናል። ችግር የመቋቋም እና የመቻል አቅማችን ተሟጧል። ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዴ እንዲህ ብሎ ነበር። “ታዋቂ መሆን አልነበረም በጣም ከባዱ ነገር ፥ ታዋቂነትን ያጎናጸፈኽን መልካም ስም ይዞ መቆየት እንጂ።” ጅል ውሳኔዎች የፍጥነት ውጤቶች ናቸው። ቶማስ ጀፈርሰን እንዲህ ይላል “ከተናደድክ እስከ አስር ቁጠር። በጣም ከተናደድክ ግን እስከ መቶ ቁጠር።” ይሄ ታላላቅ ተግባራትን የሰሩ ሰዎች ንግግር የሚነግረን የሰው ልጅ አዕምሮ ሁልጊዜ የምንመካበት እንዳልሆነ ነው። በፍጥነት ወቅት ባላንሱን ይስታል።
የሆነ ሰው ሲያናደኝ ራሴን የምጠይቀው “በዚህ ምድር ላይ ይሄ ሰው የተናገረውን ንግግር ሰምተው ምንም የማይመስላቸው ሰዎች የሉም? ልክ እኔን የተናገረኝን ቢናገራቸው ፥ ምንም እንዳልተፈጠረ የሚያልፉ የሉም? መልሴ ሁልጊዜ ማለት በሚቻል መጠን “አለ!” ነው። ስለዚህ ይሄ ነገር ግለሰባዊ (subjective) ነው ማለት ነው። የእኔ የዕይታ አድማስ መጥበብ እና የቆዳዬ ስሱነት እንጂ የሰውዬው ንግግር አይደለም ማለት ነው። ያ subjective የሆነ ግብረ መልሴ ዓለምን ከሌላ ሰው አንግል እንዳየው ያግዘኛል። ይሄ ማለት ቀላል ነው ማለት አይደለም። ፈጽሞ። ያልተገራ ውሻ ዘወትር ውስጣችን አለ።ውሻ እየበላ ያለውን ብታነሳበት ይነክስሃል። ምግቡን የሰጠኸው እና ነገም የምትሰጠው አንተ ብትሆን እንኳ።በተመሳሳይ ክብራችን፣ እንጀራችን፣ ኢጎአችን፣ ድንበራችን ፥ ተነካ ስንል ፥ እንናከሳለን። ለውሻው ራስን መግዛት እና ስለነገ ማሰብ ከባድ እንደሆነው ሁሉ ፥ እኛም ያን ማሰብ በጣም ይከብደናል።
ይሄ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያልቆመ ነገር አለ። ሰውን በንዴት እና በቅናት ተነሳስቶ ማጥቃት። ምንም እንኳ ይሄን የሚያደርጉ ሰዎች መጨረሻቸው ጸጸት እንደሆነ እያወቅን እንኳን ዛሬም ያን የሚያደርጉ ሰዎች እልፍ ናቸው።
የሒሳብ ሊቁ ብሌዝ ፓስካል “የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የሚመነጨው ፥ ሰው ብቻውን በርጋታ አንድ ክፍል ውስጥ ለመቀመጥ ባለመፍቀዱ ነው” ይላል። ሊቁ ጸጋዬ ገብረመድኅን ይሄን ግብዣ ነው ለሁላችንም ያቀረበልን። “አብረን ዝምእንበል” በሚለው ግጥሙ። “አጉል ነው ብለን ሳንፈርድ ድንቅም ነው ብለን ሳናደንቅ አስቲ ለአንድ አፍታ ዝም እንበል” ፥ መገዳደል እና መፍክር ማብዛት ለተጣባው ፖለቲካችን ምክር ሰጠን።
ዳንኤል ኮነመን “ብዙ ሰው የሚወደው ስፖርት ፥ ውሳኔ ላይ በፍጥነት መዝለል ነው (jumping to conclusion)” ይላል። ምንአልባት ያን አለማድረግ አንችል ይሆናል። ለሆነ ሰው ስልክ ደውለን ሳያነሳልን ሲቀር ፥ ንቆኝ ነው ማለት ይሆናል መጀመሪያ የሚቀለን። ምን አልባት የሆነ ነገር ፈልገን ስናጣ ፥ እከሌ ሰርቆን ነው ማለት ይሆናል የመጀመሪያው ውሳኔያችን። መጥፎ መጥፎውን ይሆናል መጀመሪያ አዕምሮአችን የሚያሳስበን። እንዲህ አስቤ ከዛ ውጤቱ ሌላ ሲሆን ፥ ራሴን “አየ አይደል!ትቸኩላለህ። ይሄ የመጀመሪያህ አይደለም። ብዙ ጊዜ እንዲህ ብለህ ከጠበከው ውጪ ሆኗል። ስለዚህ ተጠንቀቅ እለዋለሁ።” ከራሳችን ጋር መወቃቀስ እና ራሳችንን ሰው ሳይታዘበን በፊት እንታዘበው። ትላንት ተሳስተሃል። አሁንስ ልትሳሳት ብትችልስ? ስለዚህ ታገሰ። ተረጋጋ እንበለው።
ብሩስ ሊ እንዳለው ርጋታን መላበስ ፥ የትኛውንም ውጊያ የማሸነፊያ ጥበብ ነው። በሀገራችን መሪዎች ውስጥ እጅግብዙ ያሳኩ መሪዎቻችን አብዛኛው ጊዜ የሚታወቁት በታጋሽነታቸው ነው። በአጭር ሕይወታቸው የተቀጩ እንደ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ኢያሱ እና መንግስቱ ኃይለማርያም ያሉት ደግሞ ቁጡዎች እና ፈጥነው ውሳኔ መስጠት የሚወዱ ነበሩ። እነዚህ ረጅም አልመው በአጭር የተቀጩ መሪዎች ናቸው። በዘመናቸው ለሕዝባቸው ጦርነትን አብዝተው የሰጡ ነበሩ።
ታሪክ የሚነግረን መረጋጋት እና መታገስ የስኬት ጨው መሆኑን ነው። መረጋጋት ማለት ግን ውሳኔ ለመወሰን የሚቸገርን ሰው አይወክልም። የተረጋጋ ሰው መወሰን ተቸግሮ አይደለም። ይልቁንስ ውሳኔው ነው ያረጋጋው። በአዕምሮ ውስጥ ቀጣይ የሚወስዳቸው ርምጃዎች ሁሉ ግልጽ ስለሆኑለት ወይም በርጋታ ውስጥ ያልተገለጡ እና በቅርብ ሊያውቃቸው የሚገቡ መረጃዎችን እየጠበቀ ስለሆነ ነው የተረጋጋው። ንድፈ ሀሳቡን በርጋታ ውስጥ በተግባር እየፈተሸው ነው። ርጋታ ማለት ጉዞ አልባነት አይደለም። ይልቁንስ ርጋታ ማለት የድብቅ እና የስውር ሩጫ ማለት ነው። ርጋታ ማለት ንፋሱን ቁጡ እና ቀበጥባጣው ሰው እንዲሰብረው ግን አንተ ከኋላ ሆነ የደውሉን ፍጻሜ የምትጠባበቅበት ስፍራ ማለት ነው። ርጋታ ማለት ነብር በሆዱ እየቧጠጠ ወደ ሚያድነው ታርጌት ከእይታ ተሰውሮ የሚቀርበብት ሁኔታ ማለት ነው።
ርጋታ ማለት እዩኝ የሌለበት ፈጣን እድገት ማለት ነው።
Comments