- Mulualem Getachew

- 50 minutes ago
- 3 min read

የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የፓርኪንግ ጠባቂ ሆነው አሜሪካ እየሰሩ መታየታቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ አነጋግሮናል። ብዙዎች ያን የሚያክል ትልቅ ክብር ያለው ሥራ ላይ የነበረ ግለሰብ ዝቅ ብሎ፣ ሥራ ሳይንቅ መሥራቱ አስገርሟቸዋል። ለእኔ ገዱ የብዙዎቻችንን የአዕምሮን ጓዳ ጉድ ያደረገ ነው የሚመስለኝ። ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንደያዝን ነው የገለጠው። ምን ማለቴ እንደሆነ ላብራራ።
የሥራ ዓላማ ግን ምንድነው?
“አዳምንም አለው። የሚስትን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤” ዘፍ 3፥17።
በድካም ሠርቶ መብላት እንግዲህ የሚጀምረው ከዚህ ነው። እኛ የሠሪው፣ ሥራውም መልካም የሆነለት የአምላካችን እግዚአብሔር የእጆች ሥራ ነን። አዳም በገነት ውስጥ እንደማይሰራ አልተነገረንም። እንደውም ከውድቀት በፊት አዳም ሥራ ነበረው። እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት መግዛት። ዘፍ 1፥28። ሥራ የውድቀት ውጤት ነው የሚል ትምህርት ለዚህ ነው ስህተት የሚሆነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያን አይነግረንም። ነገር ግን በላቡ እና በድካም ሠርቶ መብላት የጀመረው ከውድቀት በኋላ ነው። ልጆቹም የሥራ ዘርፍ ተከፋፍለው መሥራት ጀመሩ። ከመሬት ጋር መታገል ፥ ከተፈጥሮ ጋር መታገል ጀመሩ። ፍጥረትን ያለ ችግር የሚገዛው አዳም አሁን ሁሉ ነገር በድካም ብቻ የሚሆንለት ሆነ።
ሥራ ውድቀትን ቢቀድመውም፤ ከውድቀት በኋላ ግን የሰው ልጅ ሳይሠራ መብላት እንደማይችል ተነግሮታል።
ስለዚህ መብላት የሚወድ ሁሉ መሥራት አለበት። ቢያንስ መሥራት ከልቡ መፈለግ አለበት። ቅዱስ ጳውሎስ ለዚህ ነው “ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና።” ብሎ የተናገረው። 2 ኛ ተሰሎንቄ 3፥10። ሊሠራ የማይወድ አይብላ ተብሏል።
በዚህ ምድር ሊሠራ የማይወድ ቢኖር ምግብ መስጠት እንደሌለብን ተነግሮናል። አዎ። ሊሠራ የማይወድን ምግብ እንድንከለክለው የብሉይ ኪዳን ሕግ ብቻ አይደለም የአዲስ ኪዳን የፍቅር ሕግ አዞናል። ግን አስተውሉ ሊሠራ የማይወድ ነው የሚለው። ሊሠሩ እየወደዱ በተለያዩ ምክንያቶች መሥራት የማይችሉትን ግን የመርዳት ግዴታ አለብን።
ስለዚህ ሥራ አንዱ ትልቁ ተልዕኮ ለመብላት ነው ማለት ነው።
ቅዱስ ጳውሎስን ተመልከቱ። ሊቁን ጳውሎስን። በዚህ ምድር የእውቀት ጥግ ያለውን። በመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያሉትን ሁሉ እግዚአብሔር እስከ ሦስተኛው ሰማያት ድረስ ወስዶት ያሳየውን ድንቅ ሰው። 2ኛ ቆሮ 12፥4።
ክብርን ቢሆን የእርሱን ያህል የከበረ ከመካከላችን ማን ይኖር ይሆን?! ይሄ ታላቅ ሐዋርያ ግን በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ማታ ማታ ድንኳን እየሰፋ ነበር የሚተዳደረው። ሐዋ 18፥4። ጳውሎስ ሥራን የመዘነው በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ነበር። ከሰው ሸክምነት ነጻ እስካወጣው ድረስ ፥ ሥራን አልናቀም። የወገብ በሽታ እያለበት፣ ቀኑን ሙሉ ወንጌል የመስበክ ግዴታ እያለበት ፥ ባለችው ጊዜ ግን በሰው ላይ ሸክም ላለመሆን ድንኳን እየሰፋ ራሱን ያስተዳድር ነበር።
ሌላው ፈጣሪያችን ሠራተኛ ነው። የሚበላው ጎድሎት አይደለም። እንደ እኛ አይበላም። ሌላው ላይ ሸክም ላለመሆን አይደለም። እርሱ ሁሉን የተሸከመ ነው እንጂ። ውበት እና ሞገስ አጥሮት አይደለም። እርሱ የውበት ፏፏቴ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲይ ይላል፦ “ኢየሱስ ግን። አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው።” ዮሐ 17፥5። ምንም ሳያስፈልገው፣ ማንም የሚከሰው ሳይኖር፣ ምንም ሳይጎድለው እግዚአብሔር ይሠራል። የእጆቹም ሥራ ውብ ናቸው። መልካም እና እጅግ መልካም ናቸው። እርሱ ብቻ መልካም የሆነው አምላካችን ፥ መሥራት የእርሱ መገለጫ ነው። አብ ይሠራል። ኢየሱስ ክርስቶስም ይሠራል። ያለማቋረጥ። እኛም እንድንመስለው ተጠርተናል። ስለዚህ እንሠራለን።
ለዚህ ነው የሰው ልጅ ከውድቀትም በፊት እንዲሠራ የሥራ ዘርፍ የተሰጠው። እርሱም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ማስተዳደር እና መግዛት ነበር። ሥራን የርግማን ውጤት አድርጎ ማስተማር ምንፍቅና ነው። ስሁት ትምህርት ነው።
አሁን ወደ ገዱ እንመለስ። ኢትዮጵያኖች ያለምክንያት ድሃ እንዳልሆንን አሁን እንወቅ። ያለ ምክንያት የዓለም ጭራ እንዳልሆንን አሁን ይግባን። ሥራ ክቡር ነው። በሰዎች ላይ ሸክም እንዳንሆን የሚያደርገን የእጃችን ሥራ ክቡር ነው። ለመብላት የምንሠራው ሥራችን ክቡር ነው። ከዛም እንደ ፈጣሪያችን መልካም የሆኑ ሥራዎችን ሳይቸግረን እና ሳይርበንም ጭምር የምንሠራው ክቡር ነው። ፈጣሪያችን ሠሪ ነው። እኛም እንሠራለን።
በኢትዮጵያ ግን ሥራ ሌላም ዓላማ አለው። ይሄ ግን መንፈሳዊ አይደለም። ይልቁንስ ሰይጣናዊ እንጂ። እርሱም ትዕቢት ነው።
ኢትዮጵያው ውስጥ ሥራ ስታተስ ነው። ሥራ ከባልጀራ ከፍ ማለታችንን መግለጫ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ራስን ከፍ ከፍ ማድረጊያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው እየተራበ ራሱ ፥ ሥራ ክቡር ሆኖ ሳለ የማይሰራቸው ሥራዎች አሉ። ከሊስትሮ ወይም ከቀን ሠራተኛ በብዙ እጥፍ ዝቅተኛ ገንዘብ የሚከፍል የቢሮ ሥራ ላይ መሰማራት ለኢትዮጵያውያን የተሻለ ነው። የተሻለ የሚከፍሉ እና የሰው እጅ ላይ እንዳንወድቅ ከሚያደርጉ ሥራዎች ይልቅ ዝቅተኛ እየከፈሉን የቤት ኪራይ እንኳን መሸፈን የማይችሉ ሥራዎች ላይ ተቀጥረን መቆየትን እንመርጣለን። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ትዕቢትም ነው። ሥራ ከወንድማችን የመብለጫ ማሳያ ነው። በዚህም ኢትዮጵያችን የሥራችን እርሱም የትዕቢት ውጤት ናት። አሁን ያለንበት ደረጃ የዚህ የትዕቢት ማሳያ ነው።
ትዕቢት ደግሞ ሁልጊዜ ውድቀት ይከተለዋል። ትዕቢት ባለበት ሁሉ ውድቀት ጠፍቶ አያውቅም። የዛሬይቷ ኢትዮጵያ የዚህ ውጤት ናት።
ገዱ አንዳርጋቸው ሥራዓተ መንግስቱን ብቻ አይደለም የተቃወመው። እኛን ኢትዮጵያኖችንም እንጂ። የኛንም ትዕቢት፣ የውድቀታችን መሠረትንም ጭምር ነው የገለጠው።
ወገኖቼ ማንም ራሱን በትህትና ዝቅ ለማድረግ ካላሰበ በቀር ከፍ አይልም። ትልልቅ ስኬቶች ባሉበት ቦታ ሁሉ ትህትና አለ። ይሄን ቃል ፈትኑት። ሳትቸኩሉ፣ ሳትጣደፉ ፈትሹት። ትህትናንን ከፍታ ይከተለዋል።

