- Mulualem Getachew
- 5 hours ago
- 2 min read

አሌክሳንደር ሶልዠኒስተን በአርክ ፕሌጎ ቅጾቹ ከነገርን እውነት ትልቁ የሰው ተፈጥሮ ነው። የሰው ልጅ እንዴት በቀላሉ ክፋትን፣ ፍጹም ክፋትን ወደ ማድረግ ልቡን እንደሚያሳምን ነው የሚያስረዳን። ለብዙ ጊዜ የያዝኩት አመለካከት የጀርመን ናዚዎች ያን ሁሉ አይሁዳዊ እና ከእነርሱ ውጪ ያለውን ማህበረሰብ ያጠፉበት የክፋት ጥግ ልዩ ፍጥረት እንደሆኑ አድርጌ እንድቆጥራቸው አድርጎኝ ነበር። ግን አልነበሩም። በገዳይ እና በተገዳይ መካከል ሰብአዊነትን አስመልክቶ እምብዛም ለውጥ አልነበረም። ለውጥ የነበረው አይዶሎጂው ላይ ነበር። ገዳዮች ጭልጥ ብለው በአንድ ልዩ ነን በሚል አይዶሎጂ እየተመሩ ነበር። የሚገርመው ነገር በጀርመን የሚኖሩ አይሁዶች ሳይቀሩ የሂትለርን ፓርቲ መርጠው ነበር። Appeasement ወይም ማባበል የሚባለውን ፖሊሲ ተከትለው ማለት ነው። ብንመርጠው ጥላቻውን ይቀንስልናል በሚል እምነት።
ግን አንድ ሰው አዕምሮው በጥላቻ ፖለቲካ ከታወረ በኋላ የሚያቆመው ነገር አይኖርም። ያ አይዶሎጂ ለጊዜው እስካልተሸነፈ ድረስ ጠላት ብሎ የፈረጀውን ከማጥፋት አይመለስም። በናዚ ጀርመኖች እና በአይሁዶች መካከል የአይዶሎጂ እንጂ የሰብአዊነት ልዩነት አልነበረም። ሁለቱም የሰው ልጆች ናቸው። በዛ ዓይነት ሰቆቃዊ መከራ ያለፉ አይሁዶች ዛሬ ደግሞ ሕጻናትን ለመግደል ምንም ርህራሄ ሳይኖራቸው ስታዩ ይሄ እውነት በግልጽ ይታየናል። ሳውዲ አረቢያ የመኖችን እንዴት ባለ ጭካኔ እንደጨፈጨፈቻቸው ለተመለከትን ደግሞ ተመሳሳይ ሃይማኖት ውስጥ መኖር ምንም ይሄን የሰው ክፋት የማለዘብ አቅም እንደሌለው ታያላችሁ። በትግራይ ጦርነት ወቅት የደረሰው ግፍም አንድ ሃይማኖት በሚጋሩ ሕዝቦች መካከል የተፈጸመ ግፍ ነበር።
ዛሬ አሜሪካ ውስጥ የክርስቲያን ቀኝ ዘመም ነው ስልጣን የያዘው። የክርስትና መሠረቱ ደግሞ ገና ከልጅነቱ በአምባገነኑ ሄሮድስ ተሰዶ ወደ ግብጽ ሕይወቱን ለማትረፍ የተሰደደውን ክርስቶስን ማምለክ ነው። ግን እነዚህ ክርስቲያን ነን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው አንደኛ ስደተኛ ጠል የሆኑት። ሲግመንድ ፍሮይድ ሰው የሚራመድ ተቃርኖ ነው ይላል። ክርስትና እና ስደተኛ ጠል መሆን ምንም ሳይጋጩበት መራመድ የሚችለው ሰው ብቻ ነው። የሰው ልጅን በምንም ነገር እንዲያምን ማድረግ ትችላላችሁ። ሕንድ ብትሄዱ እጅግ ብዙ የተማሩ፣ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የጫኑ ሰዎች ለከብት ሲሰግዱ ታያላችሁ። በሆነ ጉዳይ በእውቀት መራቀቁ በሆነ ጉዳይ ጅል ከመሆን የሰው ልጅን አያድነውም።
ቆሞ እያንዳንዱ የሚያደርገውን ድርጊቶች ለመፈተሽ እና በሌሎች ለመመከር ወይም ሌሎችን ለመስማት ያልፈቀደ ሰው እንደ ሸንበቆ ወጥቶ ወጥቶ በድንገት ይሰበራል። ጉደኛ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የቻለ የሰው አዕምሮ ፥ ጅል በሆኑ የጥላቻ ስብከቶች ተወስዶ በክፋት ሥራዎች ሲዝረከረክ ታዩታላችሁ። የክፋት ጥግ የፍቅር ልብ ባለው ሰው ውስጥ እንዳለ እንዘነጋለን። ሂትለር ለሕጻናት አስገራሚ ፍቅር ነበረው። ግን ይሄ ልብ አይሁዶችን ጨምሮ ሌሎች የሰው ዘሮችን ለማጥፋት የሚሆን የክፋት ጥጉን ለመፈተሽ እና ለመግራት ስላልቻለ ፥ ስልጣን ሲያገኝ መራራ ታሪክን ሠርቶ አለፈ።
ብዙዎቻችን የምንስተው የሰው ልጆች ያን የክፋት ስነልቦና አልፈውታል ብለን ነው። ያን እንዳልተሻገርነው፣ መቼምም መሻገር እንደማንችል ለማየት ጋዛ መሄድ ነው። በፍሎሪዳ ስቴት በአዞ እና አሊጌተር የተከበበው እና ስደተኞች ይታሰሩበታል በሚባለው እስር ቤት መገንበት የሚደሰተውን የነጭ ብዛት ለተመለከተ ፥ ዓለም ዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት የሚሉ ሥርዓቶችን ከመዝገቡ ሊሰርዝ እየተቃረበ መሆኑን እናስተውላለን። የጠቅላይ ፍርድ ቤቷ ዳኛ ጀስቲስ ጃክሰን እንዳለችው ዛሬ ይሄን ማስቆም ካልቻልን ፥ የአሜሪካ ሕገመንግስታዊ ሪፖብሊክ ነገ ታሪክ ይሆናል። ብዙዎቻችን ከዚህ ቀደም የነበሩ በጎ ሥርዓቶች እና ትውፊቶች እንክብካቤ እና ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ተክሎች አይመስሉንም። ያ ግን ስህተት ነው። ነቅተን ክፋት የዓለምን ብርሃን እንዳያጨልም የራሳችንን ጥረት ካላደረግን ፥ ባርነት ታሪክ ብቻ አይሆንም። ተመልሶ ይመጣል። ውሻ እና ጥቁር እዚህ አይገባም የሚለው ቀስ እያለ ስደተኛ አይገባም በሚል የስም ለውጥ እየመጣ ነው። ከዛ ከአብዛኛው ሰው በመልክ የተለየው ሁሉ ስደተኛ ይባላል። ኢለን መስክ ሲቃወማቸው ደቡብ አፍሪካነቱን እንዳስታወሱት ፥ ይሄ ማዕበል እስካልተገታ ድረስ ቅኝ ግዛት የድሮ ታሪክ ብቻ አይሆንም። ከታሪክ መጽሐፍት ወጥቶ ነገ ዜና ይሆናል። የክፋትን አቅም አቅሎ እንደማየት ሞኝነት የለም።